" Memorial"

Lemma Gutema

ለማ ጉተማ

የተከበሩ ለማ ጉተማ  

    (1934 – 1990 ዓ.ም.)      

ማን ነበሩ ?...

 

ከአባታቸዉ ከአቶ ጉተማ ደበል እና ከእናታቸዉ ከወ/ሮ ወርቅነሸ ዳኜ  ሐምሌ 10 ቀን 1934 ዓ.ም. በአርሲ ክፍለ ሀገር ፣

ጭላሎ አዉራጃ ፣ በቆጂ በምትባል ከተማ ተወለዱ ።

 

የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘዉ ኮከበ ፅባህ ት/ቤት አጠናቀቁ ።

 

በ 1951 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ባህር ባሕር ኃይልን ተቀላቅለዉ በኮሌጁ ይሰጥ የነበረዉን የእጩ መኮንንነት ትምህርት

ተከታትለዉ በማዕረግ ተመርቀዋል ።

 

ከዚህ በተጨማሪም በእንግሊዝ አገር ይሰጥ የነበረዉን ከፍተኛ የባሕር ኃይል መኮንንነት ትምህርት ተምረዋል ።

 

በቀድሞዉ ቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ የሕግ - ፋክልቲ ሲከፈት ከመጀመሪያዎቹ  የሕግ ተማሪዎች አንዱ በመሆን በ 1960 ዓ.ም.

በሕግ የባችለር ዲግሪ አግኝተዉ ተመርቀዋል ።

 

በተለያዩ የሀገር ዉስጥ እና የዉጭ ሀገራት በመዘዋወር ከፍተኛ የአስተዳደር እና ወታደራዊ ትምህርቶችን ተምረዉ

ለኢትዮጵያዉያን ወገኖቻቸዉም አስተምረዋል ።

 

ለማ ጉተማ ሀገራቸዉን ይወዱ እና ያከብሩ እንደነበረ የትምህርት ግዜያቸዉ ካጠናቀቁ በኃላ በሰሩባቸዉ እና ባገለገሉባቸዉ

ቦታዎች ሁሉ ማሳየታቸዉን ታሪካቸዉ ብቻ ሳይሆን ያገለገሉት ወገናቸዉ እና በስራ አለም አብረዋቸዉ የነበሩ ባልደረቦቻቸዉም ጭምር የሚመሰክሩላቸዉ ነዉ ።

 

 

ያገለገሉባቸዉ የስራ መስኮች በአጭሩ :

 

• በኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ኮሌጅ ዉስጥ በአስተማሪነት…

 

• የህግ ትምህርታቸዉን ካጠናቀቁ በኃላ ደግሞ በኢትዮጵያ የባሕር ኃይል  ዉስጥ በህግ አማካሪነትና በአስተማሪነት…

 

• በመለስተኛ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ቃኚ ጦር መርከብ ላይ በአዛዥነት…

 

• አሜሪካን (ሜሪላንድ) ዉስጥ በሚገኘዉ የአናፖሊስ የባሕር ኃይል አካዳሚ ከኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በመወከል በላይዘን መኮንንነት እና በአስተማሪነት…

 

• በመርማሪ ኮሚሽን በአባልነት እና በሰብሳቢነት (በኮሚሽነርነት)…

 

• በካሳ ኮሚሽን በአባልነት እና በሰብሳቢነት (በኮሚሽነርነት) …

 

• ኢትዮጵያ በምስራቅ እና በደቡብ በሶማሌ መንግስት ተስፋፊዎች ጦርነት በተከፈተባት ፈታኝ ወቅት

በሐረርጌ ክፍለ ሀገር  ዋና  አስተዳዳሪነት …

 

• በአገር አስተዳደር ሚኒስቴር በሚኒስትርነት …

 

• በአዲስ አበባ ኢ.ሠ.ፓ.አ.ኮ አንደኛ ፀሐፊነት …

 

• በአዲስ አበባ ኢ.ሠ.ፓ ኮሚቴ አንደኛ ፀሐፊነት …

 

• በጀርመን ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት …

 

• በመጨረሻም በሕ.ዲ.ሪ.ኢ የሸንጎ ምክትል ፕሬዚደንት በመሆን እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም.

በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ መንግስት በቁጥጥር ስር እንዲሆኑ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ሀገራቸዉን እና ወገናቸዉን በቅንነት አገልግለዋል።

 

እኝህ ለሀገራቸዉ እና ለሰዉ ልጆች ሁሉ ከነበራቸዉ ፍቅር የተነሳ ተወዳጅነትን ያተረፉት  ለማ ጉተማ !!...

 

ያለ ፍርድ ለሰባት አመታት በእስር ሲማቅቁ  ለነበረባቸዉ

ከፍተኛ የልብ ሕመም በቂ ሕክምና ሊያገኙ ባለመቻላቸዉ ምክንያት...

 

 

የካቲት 29 ቀን 1990 ዓ.ም. እጅግ የሚወዱትን ቤተሰባቸዉን እና ብዙ የደከሙላትን ዉድ ሀገራቸዉን  ትተዉ

ከዚህ ዐለም በሞት ተለይተዉናል ።

 

ለማ ጉተማ ከወ/ሮ ገነት ለማ ጋራ ትዳር መስርተዉ አምስት ልጆችን  ያፈሩ ዉድ አባት ነበሩ ። …

 

እኛ የዚህ ገፅ (Web site) አዘጋጆች የለማ ጉተማ ስም በተለይ ደግሞ ታሪካቸዉ !!

ተረስቶ እንዳይቀር በማሰብ ይህንን ገፅ (Web site) በስማቸዉ ከፍተንላቸዋል ።